ክቡር አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው በሃንጋሪ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላትና በሃንጋሪ ዩኒሽርስቲዎች ትምህርታቸውን ከሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር ሚያዚያ 30 ቀን 2016 በሃንጋሪ ቡዳፔስት ከተማ ውይይት አድርገዋል።
ክቡር አምባሳደር ፀጋአብ ሚያዚያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሃንጋሪ ፕሬዝዳንት ያቀረቡ ሲሆን፣ ከዚሁ ጎን ለጎን በአገራችን እየተካሄደ ስላለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ሚሲዮኑ የሚሰጣቸውን የቆንስላ አገልግሎት በተመለከተ በሃንጋሪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያይተዋል።
በወቅቱ የተገኙት የዳያስፖራ አባላት ይህ የገፅ ለገፅ የውይይት መድረክ በመመቻቸቱ ምስጋናቸውን በመግለፅ በአገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን አንስተዋል። በተለይም በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለዉ የሰላም እጦት እንደሚያሳስባቸው በመግለፅ ሰላም ለማስፈን ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም አንስተዋል። የዳያስፖራ አባላቱ በሚኖሩበት አገር በቅርበት የቆንስላ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው የጠየቁ ሲሆን፣ በሃንጋሪ ትምህርታቸውን በመከታተል የሚገኙ ተማሪዎችም መንግስት ባመቻቸው ነፃ የትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን በመግለፅ ከተማሪዎች ክፍያና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መስተካከል አለበት ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።
ክቡር አምባሳደር ፀጋአብ በዳያስፖራ አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት በሃንጋሪ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የክብር ቆንስል በነበሩት ዶ/ር ማሞ ግሩም ምትክ በሃንጋሪ የክብር ቆንስላ ለመመደብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል። በሃንጋሪ ዩኒቨርስቲዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ያነሷቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር እንደሚነጋገሩበት ገልፀዋል። የሃንጋሪ መንግስት በየዓመቱ ለ50 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ይሰጥ የነበረው የነፃ ትምህርት ዕድል በእጥፍ በማሳደግ ለ100 ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል እንዲሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል።
በመጨረሻም አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውንና ጥያቄዎችን በግልፅ በማቅረብ የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸው ተገቢና ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን በመግለፅ ሚሲዮኑም ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራትና የዳያስፖራውን ሁለገብ ተሳትፎ ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።