ክቡር አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው ዛሬ በቡካሬስት ከተማ በነበራቸዉ ቆይታ በሩማንያ በህጋዊ መንገድ በስራ ላይ ከተሰማሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን ጋር ዉይይት በማድረግ ወጣቶችን አበረታተዋል ።
በነበረዉ ዉይይትም ቋሚ መልእክተኛ ጽ/ቤቱ በሚሰጣቸው የቆንስላና ተዛማጅ አገልግሎት ዙሪያ ሰፊ ማብራርያ ተሰጥቷል።
በመድረኩ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት የገፅ ለገፅ የውይይት መድረክ በመመቻቸቱ ምስጋናቸውን በመግለፅ ሚሲዮኑ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ ከስራ ስምሪት ውል ጋር በተያያዘ ስለሚያጋጥማቸው ችግሮች እንዲሁም ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ የተለያየ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን በተለይም ዜጎች ከአገራቸው ከመውጣታቸው በፊት ስለሚሄዱበት አገር፣ ስለሚሰሩት ስራ ዓይነትና ስለሚያገኙት ክፍያ በቂ መረጃ ኖሯቸው ህጋዊ መንገድን ተከትለው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው በክቡር አምባሳደር. ተገልጿል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተሳሳተ መረጃ በመታለል በህገወጥ መንገድ ድንበር ለማቋረጥ የሞከሩ ዜጎች በችግር ላይ እየወደቁ በመሆኑ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልም በወቅቱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
ከዚህ የዳያስፖራ የውይይት መድረክ በተጨማሪ በቡካሬስት ከተማ የተከፈተ የኢትዮጵያውያን የቢዝነስ ማዕከልን በመጎብኘት በህጋዊ መንገድ በንግድ ስራ የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላቱን በማበረታታት በዚህ መንገድ ለሌሎች አርአያ ሊሆን በሚችል ስራ ላይ የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላትን ኤምባሲው እንደሚያበረታታና አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በመጨረሻም ክቡር አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው በሩማኒያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እንዲጠናክር አስፈላጊውን ዳጋፍ ኤምባሲው እንደሚያደርግና የዳያስፖራውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማጠናከር በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል።