የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር በጄኔቫ እየተካሄደ ባለው 149ኛ ኢንተር ፓርላሜንት ኅብረት (IPU) ጉባዔ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል::

ክቡር አፈ ጉባዔው በንግግራቸው በዓለም ላይ እየታየ ያለውን ፈጣን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል። በአዲሱ የሰው ሰራሽ አስተውሎ ዘመን ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ለበለጠ ሰላማዊና ዘላቂ አኗኗር ለመጠቀም የሚስችል የአስተዳደር ማዕቀፍ ማበጀት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ፤ ፓርላማው በጉዳዩ ላይ ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል::

የተከበሩ አቶ አገኘሁ ፓርላማዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዳደር ሕጋዊ ደንብ በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመጠቆም ችግሮችን ለመፍታትና የቴክኖሎጂ መሻሻል የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለማሳደግ በመንግሥታት መካከል የጋራ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል። ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመጠቀም ስነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ ለመተግበር የህብረቱ ቻርተር አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል::

የተከበሩ አቶ አገኘሁ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና ብሔራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎ ፖሊሲ ማዕቀፍን ጨምሮ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለአዎንታዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመጠቀም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ አብራርተዋል:: በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በቂ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ አለመኖር እና የአቅም ክፍተት አሁንም እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን በመግለጽ፤ የዲጂታል ሽግግርን ለማቀላጠፍ የተሻለ ትብብርና አጋርነት እንዲኖርም ጠይቀዋል።

በመጨረሻም የዘላቂ ልማት ግቦችና አጀንዳ 2030 በመላው ዓለም እንዲሳካ ህብረቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የዘወትር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል የተከበሩ አቶ አገኘሁ ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል::

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook